Wednesday, August 28, 2013

ዓሊ ቢራ፣ የሸዋሉል መንግሥቱ እና “ዮቢ ሐደሶ ሊባነታ”

ጸሓፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ
——-
ዛሬ ስለምን የማወጋችሁ ይመስላችኋል? ስለ“ፈስ” ነው የምንጨዋወተው፡፡ አዎን ስለ “ፈስ” ነው! ስለርሱ መጻፍ አይቻልም እንዴ? ስለርሱ ብንወያይ ነውረኛ እንሆናለን? የፈለጋችሁን በሉኝ! የጀመርኩትን ሳልጨርስ አላቆመም፡፡
   ደግነቱ ስለሚገማ “ፈስ” አይደለም የማወጋችሁ (ስለዚህ አፍንጫችሁን አትያዙ! ቂቂቂቂቂ….)፡፡ ስለማይገማ “ፈስ” ነው የምጽፍላችሁ፡፡ እንዲያውም ይህ “ፈስ” ባለመልካም መዓዛ ነው፡፡ ሽታው እንደ ሉባንጃ (ሊባንጃው) እና እንደ “ሊባን ፎህ” መዓዛ ያውዳል፡፡
   ወዳጆቼ! እየዘባረቅኩኝ አይደለም፡፡ እውነት ነው፡፡ መዓዛው እንደ “እጣን” የሚያውድ ፈስ አለ፡፡ እንዲህ አይነቱን “ፈስ” የሚለቅ ሰው የሚበላው ምግብ በ“ቱራበል ሚስክ” የታሸ፣ በ“አንበር” የዋጀ፣ የፓሪስ ሽቶ የተርከፈከፈበት ወዘተ… ሳይሆን ይቀራል ግን?
    ምንም አትጠራጠሩ! መዓዛማውን “ፈስ” የሚለቀው ሰውዬ እንደኛው ዓይነት ምግብ ነው የሚበላው፡፡ እንደኛው ውሃ ነው የሚጠጣው፡፡ ታዲያ “ፈሱ”ን ባለመዓዛ የሚያደርገው ምን ይሆን? እስቲ አብረን እንየው፡፡
  *****  *****  *****
  መለያየት ህመም ነው፡፡ ትልቅ ስቃይ ነው፡፡ ከምትወዱት ወዳጅና ዘመድ መለየት ደግሞ የሞት ታናሽ ወንድም ነው፡፡ አብሮ አደግ ጓደኛችሁን ወይም የምትወዱትን የቤት እመቤታችሁን በህይወት እያላችሁ ከተለያችኋቸው ስቃይና መከራው በቁም ይገድላችኋል፡፡ ታዲያ እንዲህ ዓይነቶቹን ወዳጆችና ዘመዶቻችሁን በምን ቋንቋ ነው የምትገልጹት? በሌላ አነጋገር ለርሱ/ለርሷ ያላችሁን ገደብ የለሽ ፍቅር እንዴት ብላችሁ ነው የምታስረዱት?፡
   የናንተን እንጃ! ለዚህ ጽሑፍ መሰረት የሆነውን ትውፊት ያፈለቁት የሀረርጌ ኦሮሞ ልጃገረዶች ግን ለእኩያቸው ያላቸውን ፍቅር ሲገልጹ “ዮቢ ሐደሶ ሊባነታ” ነው የሚሉት፡፡ ምን ማለት መሰላችሁ? “ውዴ/ጓዴ! አንቺ ባለእጣን መዓዛ ፈስ” እንደማለት ነው፡፡ በሙሉ ዐረፍተ ነገር ሲጻፍ ደግሞ “አንቺ የኔ ውድ ጓደኛዬ፣ እህቴ፣ ነፍሴ! ሌላው ቆርቶ ፈስሽ እኮ ለኔ እንደ እጣን ነው” እንደማለት ይሆናል፡፡
    ጥቅሉን ሐረግ ስንዝረዝረው ፍቺው የትየለሌ ነው የሚሆንብን፡፡ ለአሁኑ ግን “የኔ ውድ ባለንጀራዬ! አንቺ አብሮ አደጌ! የኔና ያንቺ መውደድ እኮ ገደብ የለውም፡፡ የመውደዳችን ጥልቀት ጥላቻን ከመሀከላችን ሰርዞታል፡፡ ሌላው ነገር ይቅርና ሰዎች ይገማል ብለው አፍንጫቸውን የሚይዙለት “ፈስ” በኔና ባንቺ መሀል ቢከሰት እንደ ሽቶና እንደ እጣን ነው የምንቆጥረው፤ ፍቅሬ! ሄዴ! ውዴ! እወድሻለሁ…” ወዘተ… እያልን ልንፈስረው (ልንፈታው) እንችላለን፡፡
   “ዮቢ ሐደሶ ሊባነታ” እያሉ ለጓደኛቸው ፍቅራቸውን የሚገልጹት የሀረርጌ ኦሮሞ ኮረዳዎች ናቸው- ከላይ እንደገለጽኩት፡፡ ይሁንና ኮረዳዎቹ በ“ዮቢ ሐደሶ ሊባነታ” አንጀቱን የሚበሉትና ልቡን የሚያብሰለስሉት ሰው ወንድ አይደለም፡፡ ሴት አብሮ አደግ ጓደኛቸውን እንዲህ የሚፈታተኑት፡፡ ይህን ግን ለሁልጊዜ እንዳይመስላችሁ፡፡ ለአንድ ቀን ብቻ የሚቆይ ትእይንት ነው፡፡ ይኸውም ባልንጀራቸው በምታገባበት ዕለት ነው፡፡
  በዚህ ዕለት ጓደኛቸው ከነርሱ ተነጥላ ከባሏ ጋር መኖር ትጀምራለች፡፡ በዘህ ዕለት በልጅነቷ አብሯት አፈር እየፈጩ የተጫወቱ፣ ወንዝ ሄደው ውሃ የቀዱ፣ ጋራ ወጥተው እንጨት የቆረጡና በታዛ ስር ስፌድ የሰፉ ጓደኞቿን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ትሰናበታለች፡፡ “የእገሌ ልጅ” መባሏ ቀርቶ “የእገሌ ሚስት” እየተባለች መጠራት ትጀምራለች፡፡ ጓደኞቿም ከርሷ ጋር እንዳሻቸው የሚሆኑበት እድል ለወደፊቱ ተመልሶ እንደማይመጣ የሚያረግጡት በዚህ እለት ነው፡፡ ስለዚህ በዚህች ታሪካዊ የመልካሙን ጊዜ ፍጻሜ  እያማረሩ በእንባ ይሸኟታል፡፡ ታዲያ ለጓደኛቸው የነበራቸውን ፍቅር ለመግለጽና የወዳጅነታቸውን ግዝፈት ለማሳየት ከ“ዮቢ ሐደሶ ሊባነታ” የተሻለ ሐረግ የላቸውም፡፡ ይህንን ሐረግ እየደጋገሙ በመምዘዝ “በኔና ባንቺ መሀል መጥፎ ነገር የለም፤ አለ ቢባል እንኳ እኔ ሁሉንም በጎ አድርጌ ነው የምመለከተው” እያሉ ይሰናበቷታል፡፡
  *****  *****  *****
እዚህ ዘንድ አንድ አስገራሚ ነገር ላጫውታችሁ፡፡
“ዮቢ ሐደሶ ሊባነታ” የኦሮምኛ ሐረግ ነው ብያችኋለሁ፡፡ በቀጥተኛ አገላለጽ “ያንቺ ፈስ ለኔ እንደ እጣን ነው እኮ” የሚል ፍቺ እንዳለውም ተናግሬአለሁ፡፡ ታዲያ “በኦሮሞ ባህል እንዲህ ተብሎ ይዘፈናልን?” የሚል ጥያቄ ሊቀርብልኝ ይችላል፡፡ መልሱ “አይቻልም” ነው፡፡ በአማርኛው ዘይቤ “ፈስ መጣብኝ” ወይንም “ፈሴን ለቀቅኩት” የሚሉት አነጋገሮች “ነውር” ተደርገው እንደሚታዩት ሁሉ በኦሮሞ ባህልም “ፈሴን ፈሳሁት” የሚለው አነጋገር የጨዋ ደንብ አይደለም፡፡ የኦሮሞ ባህል እንዲህ አይነቱን ንግግር “ሰፉ” (taboo) ይለዋል፡፡ “ሰፉ” የሆነ አነጋገር ህዝብ በተሰበሰበበት ቦታ ቀርቶ በቤት እንኳ መናገር ይከለከላል፡፡ ይሁንና የሀረርጌ ኮረዶች በግልጽ “ሐደሶ ሊባነታ” እያሉ ይዘፍናሉ! ለዚያውም በሰርግ ቤት!! ማን ፈቅዶላቸው ነው ግን?
   ነገሩ እንዲህ ነው፡፡ ኮረዶቹ (ልጃገረዶቹ) የተጠቀሙበት ቃል የኦሮምኛው “ዹፉ” አይደለም (በአማርኛ “ፈስ” ማለት ነው፤ “መፍሳት” ማለትም ይሆናል)፡፡ “ፈስ”ን ለመግለጽ የገባው ቃል የዐረብኛው “ሐደስ” ነው፡፡ በሀረርጌ ኦሮሞ ባህል በህዝብ ፊት ወይንም በአደባባይ ቢጠሩ እንደ ነውር የሚቆጠሩ ነገሮችን ሳንሸማቀቅ ለመግለጽ ከፈለግን በዐረብኛ ስማቸው ነው የምንጠራቸው፡፡ ለምሳሌ “የወንድ ብልት” ለማለት ካሻን “ዘከር” እንላለን፡፡ የሴት ብልትንም “ሐሸፋ” ብለን ብንጠራው እንደ ነውር አይቆጠርብንም፡፡ ሽንት ቤት ለማለትም “ኸላ” ማለት ይቻላል፡፡ ሰገራንም በኦሮምኛ ስሙ ሳይሆን በዐረብኛው ስም “ቦውሊ” በማለት እንጠራዋለን፡፡ (የባውሎጂ አስተማሪዎቻችን የሰው ልጅ የመራቢያ አካላትን በአማርኛ ለመግለጽ እያፈሩ፤ በእንግሊዝኛ ግን ያለምንም ፍርሃት “Penis”, “Vagina”, “Urethra”, “Testicle”, እያሉ የሚጠሩበትን ብሂል አስታውሱ)፡፡
  *****  *****  *****
  ወደ “ዮቢ ሐደሶ ሊባነታ” እንመለስ፡፡ “ዮቢ ሐደሶ ሊባነታ” አንድ ሐረግ ብቻ ነው ያለው፡፡ ነገር ግን በሰርግ ቤት “ዮቢ ሐደሶ ሊባነታ” ብቻውን አይባልም፡፡ እርሱን የሚያጅቡ ሌሎች ግጥሞች ታክለውበት በቡድን የሚዘፈን ዜማ ሆኗል፡፡
     “ዮቢ ሐደሶ ሊባነታ” እያሉ መዝፈኑን ማን እንደጀመረው አይታወቅም፡፡ የዘፈኑ ግጥሞችም ከቦታ ቦታ ይለያያሉ፡፡ ዜማውም ሊለያይ ይችላል፡፡ ነገር ግን አዝማቹ ምንጊዜም ቢሆን አንድ አይነት ነው፡፡ እርሱም ባለሁለት መስመር ነው፡፡ እንዲህ ይሄዳል፡፡
    “ዮቢ ዮቢ ዮቢ ሐደሶ ሊባነታ
     ወይ ነገየቲ ናን ጄኢ ሂሪዮ አማነታ”
     ግጥሙን ከነነፍሱ በአማርኛ መፍታት በጣም ይከብዳል፡፡ ነገር ግን እንዲህ ሊባል ይችላል፡፡
“ውዴ ጓዴ የሌለብሽ እንከን
  ያንቺ ሐደስ እኮ ነው የኔ እጣን
 ደህና ሁኚ በይኝ ውዴ አደራሽን”
 (“ሐደስ”ን ሳንፈታው እንዳለ ብንወስደው ይሻላል)
ታዲያ “ዮቢ ሐደሶ ሊባነታ” በሀረርጌ ገጠሮች ብቻ ተወስኖ አልቀረም፡፡ እጅግ ውብ ጣዕም ባለው ዜማ ተቀምሮ ለኢትዮጵያ ህዝብ ቀርቧል፡፡ ለዚያውም ከ30 ዓመታት በፊት! የሚገርመው ታዲያ ያኔ “ዮቢ ሐደሶ ሊባነታ” እያለ የዘፈነው ሴት አይደለም፡፡ አንጋፋው አርቲስት ዶ/ር ዓሊ ቢራ ነው! ይህ ትንግርት እንዴት ሊፈጠር ቻለ?
    መልሱን ለማወቅ ካሻችሁ ከሁለት ቀናት በፊት (ሰኞ ነሐሴ 19/2005) በጻፍኩት ጽሑፍ ስራዋን በመጠኑ ያስተዋወቅኳችሁን ጋዜጠኛና ደራሲ የሸዋሉል መንግሥቱ የግዴታ ማንሳት ይኖርብናል፡፡ ምክንያቱም “ዮቢ ሐደሶ ሊባነታ”ን ዓሊ ቢራ በዘፈነው መልኩ አቀናብራ ዘፈን እንዲሆን ያረገችው እርሷ ናትና!
   የሸዋሉል መንግሥቱ የሀረርጌ ተወላጅ ናት፡፡ በምስራቁ የኦሮሞ ባህል ውስጥ ነው ያደገችው፡፡ በሀረርጌ ገጠሮች ሴቶች “ዮቢ ሐደሶ ሊባነታ”ን ሲዘፍኑ አይታለች፡፡ እነዚያ ኮረዳዎች ጓደኛቸው በትዳር ስትለያቸው “እስከ ወዲያኛው ተለያየን” እያሉ በእንባ እንደሚሸኟት ታውቃለች፡፡ ዘፈኑን ለዓሊ ቢራ የሰጠችበትን መነሻ ለጊዜው በትክክል ባናውቀውም ድርሰቱን ስትጽፈው የነዚያ ኮረዳዎች እንባ እየታያትና የመለያየትን ክፉ እጣ እያሰበች እንደሆነ ለመረዳት አይከብደንም፡፡ በዚህም የመለያየትን አስከፊነት በሚገባ ለመግለጽ ችላለች፡፡ ለዚህ ቀላሉ አብነት በዘፈኑ ግጥም ውስጥ የሚታየው የእንጉርጉሮ ሀቅታና የሐዘን ድባብ ነው፡፡ እስቲ ሙሉ ግጥሙን ልጻፍላችሁ (በነገራችን ላይ የሸዋሉል ባለ ሁለት መስመሩን አዝማች ሰፋ አድርጋ ባለ አራት መስመር አድርገዋለች፤ ስለዚህ ቀጥዬ የምጽፍላችሁ ባህላዊውን ግጥም ሳይሆን እርሷ የጻፈችውን ባለ አራት መስመሩን ግጥም ነው)፡፡
——–
አዝማቹ
Way yoobi yoobi yoobi hadasoo libaanta (ውዴ ባለ መዓዛማው “ሐደስ”)
Way yoobi yoobi bal’oo hiriyoo imaanta (ውዴ ጓዴ አደራችን አይገሰስ)
Wa nagayatti nan je’i hiriyoo ta dhaammata (እስቲ ለስንብትሽ ደህና ሁን በይኝ)
Way eenyu eenyu eenyu hiriyoo nayaadata  (አንቺ ከሄድሽማ ማን ነው የሚያስታውሰኝ)
Hiriyoo nagaafata (ማን ነው የሚጠይቀኝ)
———-
Guyyaan naaf hindhihu halkan naaf hinbari’u (አይነጋልኝም ሌቱ ቀኑም አይመሽልኝ)
Koottu mee yaa boontuu simalee naaf hintahu (እስቲ ነይ የኔ ውድ ያላንቺ አይሆንልኝ)
Si laalu si hin’argu siyaamu hin awwaatu (በዐይኔም አላይሽ ብጠራሽ አትሰሚኝ)
Naduraa fagaatte iddoon ati jirtu (ያለሽበት ቦታ እንደዚህ ርቆኝ)
Osonin si eegu nin seena ninbaha (አንቺን እያየሁ እገባና እወጣለሁ)
Yaadni kee narakke ani akkamin taha (ናፍቆትሽ አስጨነቀኝ እንዴት ነው የምሆነው?)
     *****  *****  *****
ዓሊ ቢራ ከዛሬ ስምንት ዓመት በፊት በኤፍ ኤም የቅዳሜ ጨዋታ ፕሮግራም ከመዓዛ ብሩ ጋር ባደረገው ቃለ-ምልልስ ስለዘፈኑና ስለደራሲዋ ማውሳቱ ትዝ ይለኛል፡፡ ነገር ግን ያኔ እርሱ የጠቀሳት የግጥሙ ደራሲ የሸዋሉል መንግሥቱ መሆኗን ልብ አላልኩትም፡፡ ነገሩን በቅርብ ጊዜ ባደረግኩት ምርመራ ነው የደረስኩበት፡፡ ያቺ ውድ ደራሲና ጋዜጠኛ ከዓሊ ቢራ ጋር ብቻ ሳይሆን ከበርካቶች ጋር ሆና ዘመን አይሽሬ የጥበብ ስራዎችን ሰርታለች፡፡ ይሁንና በዘመነ ቀይ ሽብር የመኢሶን አባል ሆና በመገኘቷ የጥይት እራት ሆነች፡፡ የርሷን ሞት ተከትሎ የተነዛው የአንድ ወገን ወሬም የጥበብ ስራዋን ሸፍነው፡፡ ይህ ትውልድ ግን ለጥበብ ውሎዋ ተገቢውን እውቅና የመስጠት ሀገራዊ ግዴታ አለበት፡፡ እንደዚያ ካደረግን የዛሬዎቹ ጠቢባንም ለነገው መዘክራቸው ዋስትና አገኙ ማለት ነው፡፡ ታሪክም ትክክለኛ ሚናውን የሚጫወተው ያኔ ነው፡፡
  ——
አሁን አበቃሁ፡፡ ከላይ በመግቢያዬ ስለዚያ ነገር (“ፈስ”) ሳወራ አብሽቄአችሁ ከሆነ በይቅርታ እለፉኝ፡፡ ግን እኮ አጨራረሴ ጥሩ ነው! አይደለም እንዴ? ጥሩ ነው ካላችሁ ይሁን! ጥሩ ካልሆነም ለወደፊቱ እናሻሽላለን፡፡
 ለማንኛውም በወዳጅነታችን እንሰንበት
 አፈንዲ ሙተቂ
ነሐሴ 22/2005    source  ( http://www.gulelepost.com/2013/08/28/hadasoo-libaanataa/ )

No comments:

Post a Comment